በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ ሴት አካል ጉዳተኞች የሚደርስባቸውን ጫና እና የተዛባ አመለካከት ለመቅረፍ ሴት የምክር ቤት አባላት ትልቅ ጉልህ ሚና አላቸው፦የተከበሩ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ
(ሰኔ፤06/2017 ዓ.ም) በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ ሴት አካል ጉዳተኞች የሚደርስባቸውን ጫና እና የተዛባ አመለካከት ለመቅረፍ ሴት የምክር ቤት አባላት ትልቅ ጉልህ ሚና እንዳላቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማህበር ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሴት ምክር ቤት አባላት የአካል ጉዳተኛ ሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ዙሪያ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠና መድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ ሴት አካል ጉዳተኞች የሚደርስባቸውን ጫና እና የተዛቡ አመለካከቶች እንዲቀረፉ ሴት የምክር ቤት አባላት ድምፅ የመሆን ትልቅ ጉልህ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
ሴት አካል ጉዳተኞች ሁሉንም እችላለሁ የሚል ቆራጥ እሳቤ እንዲኖራቸው ሴት የምክር ቤት አባላት ከስልጠና መልስ በኋላ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አፈጉባኤዋ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የትኛውንም የተዛባ አመለካከት ማስተካከል የምንችለው እኛው ሴቶች ነን ያሉት አፈጉባኤዋ ከስልጠናው የተገኘውን ግንዛቤ ውጤት ላይ ማድረስ ቅድሚያ የሚሰጠው ሀላፊነት እንደሆነም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ድባቤ ባጫ በበኩላቸው አካል ጉዳተኛ ሴቶችን በማብቃት በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ዘርፍ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ወደ መሪነት እንዲመጡ ሴት የህዝብ ተመራጮች ሀላፊነቱን ወስደው በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ማህበሩ በሴት አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሱ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖዎችን ለመቅረፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ወ/ሮ ድባቤ ባጫ ገልፀዋል።